በመኪና አደጋ የተጎዳን ግለሰብ ህክምና ሳያገኝ መንገድ ላይ ጥለው የተሰወሩ ግለሰቦችንና ተባባሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አስታወቀ፡፡

Thursday, 10 July 2025 06:22
በመኪና አደጋ የተጎዳን ግለሰብ ህክምና ሳያገኝ መንገድ ላይ ጥለው የተሰወሩ ግለሰቦችንና ተባባሪዎችን ይዞ ምርመራ እያጣራ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምርያ አስታወቀ፡፡
***
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 30 ቀን 2017 ዓ/ም (አዲስ ፖሊስ)፦ ሰኔ 9 ቀን 2017 ዓ/ም ከቀኑ 8 ሰዓት ተኩል ላይ የሰሌዳ ቁጥሩ ኮድ 2A አዲስ አበባ 73886 አይነቱ ፕላትዝ የሆነ ተሽከርካሪን የምታሽከረክር ግለሰብ ከዊንጌት ወደ አስኮ በመጓዝ ላይ እያለች ጨረታ እየተባለ ከሚጠራው አካባቢ አንድ እግረኛ ላይ ጉዳት ታደርሳለች፡፡
አደጋ አድራሿ በአካባቢው ከነበሩ ግለሰቦች ጋር በመተባበር አደጋ የደረሰበትን ተጎጂ በአቅራቢያቸው ወደሚገኝ የግል የህክምና ተቋም ይዘውት እንደሄዱና ካርድ ካወጡ በኋላ የተጎጂው ማንነት የሚገልፅ መታወቃያ የሌለው በመሆኑ እርዳታ ለመስጠት እንደሚቸገሩና ወደ ሌላ ሆስፒታል ይዛው እንደሄዱ ግለሰቧ ለፖሊስ ከሰጠችው ቃል ማወቅ ተችሏል ።
አሽከርካሪዋ ያጋጠማትን ችግር ለባለቤቷ በስልክ ደውላ ማሳወቋን ተከትሎ ባለቤቷ ከጓደኛው ጋር በመምጣት እሷን በሌላ መኪና ወደቤቷ በመሸኘት የአደጋ አድራሿ ባለቤትና ጓደኛው ተጎጂውን ይዘው ይሄዳሉ፡፡
በምርመራ መዝገቡ እንደተገለፀው ግለሰቦቹ ተጎጂውን ይዘውት ከሄዱ በኃላ ከአሁን አሁን ይነቃል በሚል ምንም አይነት ህክምና ሳያገኝ እስከ ምሽቱ 2፡00 ሲጠባበቁ ቆይተው ባለመንቃቱ አራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው አቧሬ ተብሎ ከሚጠራው ስፍራ ጭር ያለ ቦታ አጥር ጥግ ጥለውት መሰወራቸው ተረጋግጧል። ተጎጂው በወደቀበት አድሮ ዝናብ አበስብሶት ጠዋት ላይ የአካባቢው ሰዎች ለፖሊስ ሪፖርት ያደርጋሉ፡፡ ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ ግለሰቡ ወደ ሆስፒታል እንዲሄድ ካደረገ በኃላ ባደረገው ምርመራ የማስፋት ሥራ በአደጋው ወቅት ተጎጂው ህክምና እንዲያገኝ ከአሽከርካሪዋ ጋር በመተባበር ተጎጂውን ወደ ህክምና ተቋም ያደረሱ ሰዎች በማግኘት ስለ አደጋው ሁኔታ ተጨማሪ መረጃ በመቀበል ባደረገው ክትትል አደጋ ያደረሰችውን አሽከርካሪ፣ ባለቤቷን እንዲሁም ከፖሊስ ማስረጃ ሳያገኝ አደጋ ያደረሰውን ተሽከርካሪ የፊት መስታወት የቀየረን ግለሰብን ይዞ ምርመራው መቀጠሉን እና አንድ ተጠርጣሪን ለመያዝ ክትትል እያደረገ መሆኑን የጉለሌ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል፡፡
የህክምና ተቋማት በትራፊክ አደጋ ጉዳት የደረሰበትን ግለሰብ የማከም እንዲሁም ስለ አደጋው ለፖሊስ ሪፖርት የማድረግ ኃላፊነታቸው በአግባቡ መወጣት እንዳለባቸውና አሽከርካሪዎችም የትራፊክ ተጎጂዎች ህክምና እንዲያገኝ የማድረግ ግዴታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ ፖሊስ አሳስቦ ጋራዥ ቤቶችም እንደ አደጋው ሁኔታ ከፖሊስ ሪፖርት ሳያገኙ የሚያደርጉት ጥገና የህግ ተጠያቂነትን የሚያስከትል መሆኑን ማወቅ እንዳለባቸው ፖሊስ መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
የአደጋው ተጎጂው ህክምና እየተደረገለት እንደሚገኝም የአዲስ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጨምሮ ገልጿል።
*
ዘገባ:-ኢንስፔክተር እመቤት ሃብታሙ
*
ለፖሊሳዊ መረጃዎቻችን፦
በቴሌግራም:- https://t.me/addispolice
በትዊተር፦Twitter https://twitter.com/AddisPolice
ድረ ገጽ፦ web https://www.addispolice.gov.et/
“በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል!”
“Protect with courage, Serve with Compassion!”
Rate this item
(0 votes)

Leave a comment

Make sure you enter all the required information, indicated by an asterisk (*). HTML code is not allowed.

የቪድዮ ክምችት

ቪድዮዎች

በብዛት የታየ ቪድዮ

አሽከርክር ረጋ ብለህ

ፎቶዎች

Social Media

fbtwitteryoutubegoogleplus