ደሞዝ አልከፈልከኝም በሚል ምክንያት አሰሪውን የገደለ ወንጀለኛ በ21አመት ፅኑ እስራት ተቀጣ፡፡
***
አዲስ አበባ፤ ሰኔ 20 ቀን 2017 ዓ/ም (አዲስ ፖሊስ)፦ ተከሳሹ ጌቱ መስፍን ይባላል፤ የወንጀል ድርጊቱን የፈፀመው ነሀሴ 27 ቀን 2014 ዓ/ም ከረፋዱ 4 ሰዓት ከ30 ሲሆን በቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ 10 ለገሃር ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ ኖህ ሪል ስቴት ከሚያሰራው ህንፃ 16ኛ ጅምር ፎቅ ላይ ነው።
ሟች ሀጂብ ያሲን የተባለው ግለሰብ ከኖህ ሪል እስቴት ኮንትራት በመውሰድ ከስሩ በርካታ ሰራተኞችን ቀጥሮ የሚያሰራ ግለሰብ ነው።
ነሀሴ 27 ቀን 2014 ዓ/ም የዘወትር ስራውን ለማሰራት ሰራተኞችን ወደ የስራቸው ያሰማራል። ተከሳሽም ሟች የነበረበት ቦታ ጭር ማለቱን እና ማንም አለመኖሩን እንደ ጥሩ አጋጣሚ በመውሰድ ደሞዜን ከለከልከኝ በሚል ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት ሟች ሀጂብ ያሲንን ስራ እየሰራ ባለበት 16ኛ ፎቅ ላይ በፌሮ ብረት ግንባሩን በመምታት እና አንገቱን በሽቦ ገመድ በማነቅና በማሰር ህይወቱ እንዲያልፍ በማድረግ ሟችን ከህንፃው ተሸክሞ በማውረድ የህንፃው መሰረት ስር የሚገኝ የተጠራቀመ ውሃ ውስጥ አስከሬኑን በመጣል ከአካባቢው ይሰወራል።
የወንጀሉ መፈፀም ሪፖርት የደረሰው ፖሊስ የምርመራ ክፍሉና የክትትልና ኦፕሬሽን ቡድኑ በመዋቀርና በመቀናጀት ወንጀል ፈፃሚውን ለመያዝ በተደረገ ጥረት ተከሳሽ ጌቱ መስፍን ወንጀሉን ከፈፀመ በኋላ ምንም እንዳልተፈፀመ በኔጌሌ ቦረና ከተማ በአንድ ተቋም ውስጥ ተቀጥሮ በመስራት ላይ እንዳለ በቁጥጥር ስር ሊውል መቻሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ገልጿል።
በተከሳሽ ጌቱ መስፍን ላይ የምርመራ መዝገቡን በሰውና በሰነድ ማስረጃ በማጠናከር ለሚመለከተው የፍትህ አካል በመላክ ክስ እንደተመሰረተበት የገለፀው የአዲስ አበባ ፖሊስ ተከሳሽ ጌቱ ጥፋተኛ ሆኖ በማግኘቱ የፌዴራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት ልደታ ምድብ 2ኛ ግድያና ከባድ ውንብድና ወንጀል ችሎት በ21 አመት ፅኑ እስራት እንዲቀጣ እንደተወሰነበት ገልጿል።
ማንም ሰው ወንጀል ፈፅሞ ከህግ እና ከማህበረሰቡ ማምለጥ እንደማይቻል የአዲስ አበባ ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ጠቅሶ ያለመግባባት በሚፈጠርበት ወቅት በመነጋገር መፍታት ይገባል ሲል መልዕክቱን አስተላልፏል።
*
ዘገባ :- ኢንስፔክተር እመቤት ሃብታሙ
*
ለፖሊሳዊ መረጃዎቻችን፦
በቴሌግራም:- https://t.me/addispolice
በትዊተር፦Twitter https://twitter.com/AddisPolice
ድረ ገጽ፦ web https://www.addispolice.gov.et/
“በጀግንነት መጠበቅ በሰብዓዊነት ማገልገል!”
“Protect with courage, Serve with Compassion!”