በዓለም አቀፍ ለ31ኛ ፤ በሀገር አቀፍ ለ30ኛ ጊዜ የተከበረውን የኤች.አይ.ቪ ኤድስ ቀን ምክንያት በማድረግ ለፖሊስ አመራሮችና አባላት የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጠ፡፡
የስልጠናው ተከፋዩች በፈቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የደም ልገሳ እና የኤች.አይ.ቪ ምርመራ አደረጉ፡፡ "ለኤች.አይ.ቪ ኤድስ ይበልጥ ተጋላጭ ነን፣ እንመርመር እራሳችን እንወቅ" በሚል መሪ ቃል ህዳር 28 ቀን 2011 ዓ.ም በኮሚሽኑ የመሰብሰቢያ አዳራሽ በተዘጋጀው የግንዛቤ ማሥጨበጫ ፕሮግራም ላይ የተገኙት የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ዘላለም መንግስቴ ጤንነቱ የተጠበቀ የህዝብ አገልጋይ የፖሊስ አባላት እንዲኖር ኮሚሽኑ አበክሮ እንደሚሰራ ገልፀው ሁሉም አመራርና አባላት ከተላላፊ በሽታዎች እራሳቸውን መጠበቅ እንዳለባቸው መልእክት አሳስበዋል፡፡
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽ/ቤት ኃላፊ ሲስተር ብርዛፍ ገብሩ በበኩላቸው ኤች.አይ.ቪ/ ኤድስ በሀገራችን በርካታ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳቶችን እያስከተለ መሆኑን አስታውሰው በተለይ ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል በቫይረሱ እየተጠቃ ስለሆነ ስርጭቱን ለመግታትና ለመቆጣጠር ሁሉም ዜጋ የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ሲሉ የበሽታው ሰለባ መክረዋል፡፡
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የሰው ሀብት ልማት አስተዳደር ዳይሬክቶሬት ረ/ኮሚሽነር ዮሐንስ ጭልጆ አብዛኛው የኮሚሽኑ አባላት በወጣትነት የዕድሜ ክልል የሚገኙ በመሆናቸው ራሳቸውንና ሌሎችን ከኤች. አይ. ቪ ኤድስ በመከላከል ሀላፊነታቸውን መወጣት ይኖርባቸዋል ብለው ኮሚሽኑ ከአዲስ አበባ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከልና መቆጣጠር ፅ/ቤት ጋር ያለውን ቁርኝት አጠናክሮ በመቀጠል መሰል የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል፡፡
ማዕከልን ጨምሮ ከአስሩ ክ/ከተማ ፖሊስ መምሪያ ለተውጣጡ አመራርና አባላት በቅድመ መከላከል ዙሪያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የኤች.አይ.ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ጽ/ቤት ባለሙያ በሆኑት ሲስተር ሽብሬ መንገሻ አማካኝ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና ተሰጥቷል፡፡
በሌላ መልኩ የፖሊስ አመራር እና አባላቱ በደም እጦት ምክንያት ወገኖቻችን ህይወቻችን እንዳያጡ ለኢትዮጵያ ደም ባንክ አገልግሎት ደም የለገሱ ሲሆን በፍቃደኝነት ላይ የተመሰረተ የኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ምርመራ አድርገዋል፡፡