በአ/አበባ ከተማ በተለያዩ ክ/ከተሞች ጊዜ ተወስዶ በተደረገ ሰፊ ጥናት ፖሊስ በቁጥጥር ስር ያዋላቸው ተጠርጣሪዎች በ88 የተለያዩ የወንጀል ፈፃሚዎች ቡድን የተደራጁ 216 ግለሰቦች መሆናቸውን የገለፁት በኮሚሽኑ የኢኮኖሚና የልዩ ልዩ ወንጀሎች ዲቪዚዮን ኃላፊ የሆኑት ኮማንደር አበራ ቡሊና ናቸው፡፡
ሐምሌ 30 ቀን 2009 ዓ/ም በቢሯቸው በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳብራሩት ጊዜ በወሰደው ጥናት ከቅሚያ ወንጀል ጀምሮ በርካታ ቁጥር ያለው የተለያዩ ሀገራት ገንዘቦችና የኢትዮጵያ ብር እንዲሁም የተለያየ ደረጃ ያላቸው አደንዛዥ እፆች ከግለሰቦቹ ጋር ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ጨምረው ገልፀዋል፡፡
ለስራው ውጤታማነት ህብረተሰቡ መረጃ በመስጠትና ጥቆማ በማድረግ ያደረገው ትብብር ከፍተኛ አስተዋፅኦ እንደነበረው የገለፁት ኃላፊው ፖሊስ የምርመራ መዝገብ አደራጅቶ ለሚመለከተው የፍትህ አካል ለማቅረብ በዝግጅት ላይ ነው ብለዋል፡፡
መሰል የወንጀል ድርጊቶች በሀገር ኢኮኖሚ ላይ የሚያስከትሉት ተፅእኖ ከፍተኛ በመሆኑ ፖሊስ ቀጣይነት ያለው ሰፊ ጥናቶችን በማድረግ ወንጀል ፈፃሚዎች በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያደርገውን ጥረት አጠናክሮ ይቀጥላል ሲሉ ገልፀው የህብረተሰቡ ትብብር በቀጣይነትም ለፖሊስ ስራ ወሳኝ በመሆኑ ትብብሩ እንዲቀጥል መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡